ማኅበሩ የአምቡላንስና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ


የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ተራድኦ የጋራ ብልፅግና አገራት ድርጅትጋር በመተባበር በደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን አምቡላንሶችና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የተደረገውንም ድጋፍ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን እና ድጋፍ ለተደረገላቸው ወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች አስረክቧል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በ90 ዓመታት በርካታ ሰብዓዊ፣ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ያከናወነ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ቅንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ቸኮል ገልጸው፤ማህበሩ ባለፉት ዓመታት አገልግሎትን በማስፋፋትና በማጠናክር እየሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል። እያንዳንዳቸው 18 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው ሁለት አምቡላንሶች ለተንታ ወረዳ እና ለለጋምቦ ወረዳ ድጋፍ መደረጉን አክለዋል።
በተጨማሪም ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ተራድኦ የጋራ ብልፅግና አገራት ድርጅት ጋር በመተባበር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው በለጋምቦና ጃማ ወረዳ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድሀኒት፣የህክምና ቁሳቁስና ማሽነሪ ድጋፍ ስለመደረጉም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር በስሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ከዚህ ቀደምም አምቡላንሰ ፣ በፀሐይ ጉልበት የሚሰሩ የመጠጥ ውኃና መሰረተ ልማትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ያውሱት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ናቸው::

አምቡላንስ ድጋፍ መደረጉ በወሊድ ምክንያት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል። አምቡላንሶቹ ለድንተኛ አደጋ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ቁሳቁስ የተሟላቸው ዘመናዊና ምቹ መሆናቸውንም ነው አቶ ጌታቸው የጠቀሱት።
የመድሀኒት እና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፎቹም በጤና ተቋማት የነበውን እጥረት መቅረፍ ስለሚችሉ የማኅበረስቡን እንግልት ከመቀነሱም በላይ በቀጠይ ለጤና ተቋማቱ የፋይናንስ ግብኣት ምንጭ እንደሚሆኑ አቶ ጌታቸው አመልክተዋል። ድጋፎቹ በአግባቡ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን እንዳሉት ደግሞ የአምቡላንሶቹ ድጋፍ እናቶችና ህጻናትን ጨምሮ አደጋ የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ በዞኑ የነበረውን እጥረት ያቃልላል።

የመድሀኒት ድጋፍም ከዋጋ ጋር ተያይዞ በጤና ተቋማት የነበረውን የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ነው አቶ አሊ የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በብዙ ነገሮች እየደገፈ በመሆኑ በእጅጉ ሊመስገን ይገባል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አቶ አሊ መኮንን።
በድጋፋ ከመድሀኒት በተጨማሪ አልትራ ሳውንድ፣ ኬሚስትሪ ማሽን፣ ማይክሮስኮፕ፣ የደም መመርመሪያ እና መሰል ከማዋላጃ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።
ዘገባው የደቡብ ወሎ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ነው