የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በአጭር የሞባይል መልዕክት የአባላት ምዝገባ ሊጀምር ነው
February 18, 2019
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ 6546 አጭር የፅሁፍ መልዕክትን በመጠቀም የአባላት ምዝገባ እና የእርዳታ ማሰባሰብ ስራዎችን ሊጀምር ነው፡፡ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ይህን ይፋ ያደረገው የካቲት 05 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡
የቅርንጫፉ ኃላፊ አቶ አበባው በቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ላለፉት 38 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረው የቤት ለቤት የአባላት ምዝገባ ዘዴ ኋላ ቀር በመሆኑ ይህን አጭር የፅሁፍ መልዕክት መጀመር በርካታ ሰዎች አባል እንዲሆኑና የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ሚርጌሳ ካባ የቅርንጫፉ ቦርድ ሊቀመንበር በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ የተለያዩ ሀገራዊና አለምአቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ መሆኗን ገልፀው አጭር የፅሁፍ መልዕክቱን መጠቀም የቅርንጫፉን አባላት ቁጥር ለመጨመር እና ሀብት ለማሰባሰብ የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ኢትዮ ቴሌኮም ላደረገው ድጋፍ የቦርድ ሊቀመንበሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ማንኛውም ሰው በ6546 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ያለምንም ክፍያ ከተመዘገበ በኋላ በ6547 አባል ሆኖ መመዝገብ እንዲሁም በ6548 ደግሞ የፈለገውን መዋጮ በማድረግ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሚያከናውናቸውን ሰብዓዊ ተግባራት ማገዝ እንደሚቻል ታውቋል፡፡
አጭር የፅሁፍ መልዕክቱ አገልግሎት ከሳምንት በኋላ በይፋ እንደሚጀምር በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ካሉት አጠቃላይ 6.1 ሚሊዮን አባላት ውስጥ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ወደ ሁለት መቶ ሺህ አባላት እንዳሉት አቶ አበባው ገልፀዋል፡፡