ማኅበሩ የሀገር ውስጥ ሀብት የማሰባሰብ ጥረቱን እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ማኅበሩ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል ሲያከብር የተገኙት ክብርት የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት እና የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደተናገሩት ማኅበሩ ከሀገር ውስጥ የሚገኘውን ድጋፍ የማጠናከር እና የአባላቱን እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ ሊያስቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የዘንድሮ የዓለም ዓቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ‘ፍቅር’ በሚል መሪቃል የተከበረ ሲሆን ማኅበሩ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ‘ሠብዓዊነት ለሠላም’ በሚለው መሪ ቃል አክብሯል፡፡ የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘወዴ እንደተናገሩት ‘ዛሬ ሠብዓዊነት፣ ሠላም እና ልማት መካከል ያለው ከፍተኛ ትስስር እና ተመጋጋቢነት ግልፅ ሆኖ የመጣበት እና ቀጣይነት ያገኘበት ግዜ ነው፡፡ በእነዚህ ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ያለው ትስስር ያመላከተው ዋና ጉዳይ ቢኖር ከሶስቱ አንዱ ብቻውን ዘላቂ መፍትሄ ሊያስገኝ እንደማይችል ነው’፡፡ በመሆኑም ሠብዓዊነትን ከሠላም፣ ልማት እና ሰብዓዊ መብት ጋር አስተሳስሮ ማስኬድ የማኅበሩ ሌላኛው የትኩረት መስክ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የማኅበሩ መሠረታዊ መርህ እና ተግባር በየትኛውም ስፍራ እና በማንኛውም ግዜ የሰውን ልጅ ከመከራ እና ስቃይ መከላከል እና ማቃለል ነው ያሉት የኢቀመማ ዋና ፀሀፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋ አረጋ ማኅበሩ በተሻለ ተቋማዊ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ሁለንተናዊ የለውጥ ዕቅዶችን እንደተጀመረ እና ሠፊ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እንቅስቃሴውን ከመደገፍ አኳያ ማኅበሩ የህዝብ እንደመሆኑ በአመዛኙ በአገር ውስጥ ሀብት የተደገፈ እንዲሆን ስልት እና አደረጃጀት እንደተቀረፀም ገልፀዋል፡፡ ይሄም ከጥቂት ሣምንት በኋላ በክብርት ፕሬዝዳንቷ እና በማኅበሩ የበላይ ጠባቂ የሥራ መመሪያ ይጀመራል፡፡
በመድረኩ ላይ እንደተገለፀው ማኅበሩ ባለፉት 4 ወራት ብቻ ከብር ከ40 ሚሊዮን በላይ በማሰባሰብ በደቡብ ክልል ጌዲኦ እና ባስኬቶ፣ በኦሮሚያ ጉጂ እንዲሁም በአማራ ክልል አርማጭሆ፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ትክል ድንጋይ ፣ ዓይን አምባ እና መተማ ዩሀንስ አካባቢዎች ለወገኖች እርዳታ መስጠት እንደተቻለ ታውቋል፡፡ በዚህ ግዜ ቤት ለቤት እርዳታ አሰባስበው ለማኅበሩ እርዳታ ካደረጉ የቦሌ አካባቢ ወረዳ 8 እናቶችን ጨምሮ ጉልበታቸውን፣ ግዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን ለለገሱ የማኅበሩ አባላት፣ በጎ ፈቃደኞች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ባለሀብቶች፣ የሙያ ማኅበራት እና ግለሰቦች የማኅበሩ የበላይ ጠባቂያችን ምስጋና አቅርቧል፡፡ በተመሳሳይ በሂልተን የበዓሉ አከባበር ላይ በኢትዮጵያ ሰዓልያን ማኅበር በኩል የታዋቂ ሰዓልያን የጥበብ ውጤቶች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን፤ ከሽያጭ የሚገኘው ገቢ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንደሚውል ተገልጿል፡፡