ማኅበሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የኮቪድ-19 ወይም ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም በማኅበሩ ዋና ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ዋና ፀሀፊ ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል 16 የማኅበሩ በጎ ፈቃደኞች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቡድን ጋር በመሆን በአዳማ፣ በአሰላ እና ዴራ ከተሞች ለቫይረሱ ማፅጃ ኬሚካል ርጭት ማካሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ4000 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በእምነት ተቋማት፣ ገበያ ቦታዎች፣ ባንኮች፣ የትራንስፖርት ማዕከላት፣ በትላልቅ ሆቴሎችና ህዝብ በብዛት በሚከማችባቸው ሥፍራዎች ከ3825 በላይ በራሪ ፅሁፎቹን በማሰራጨት ስለ ቫይረሱ ምንነት፣ መተላለፊያ መንገድና መከላከያ ዘዴዎች እንዲሁም የበጎፈቃደኞች ደህንነትና ሚና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ፈቃደኞች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት በአውሮፕላን ማረፊያዎችና ከአጎራባች ሀገራት መግቢያ ኬላዎች ላይ የሙቀት ልየታ እና የተዋስያን ማንፃት፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እጅ የማስታጠብ፣ በትልልቅ ከተሞች በአምቡላንስ የታገዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ከነማ መድኃኒት ቤቶች ከ100 በላይ በጎፈቃደኞችን በማሰማራት የማስተባበር ሥራዎች እንዲከናውኑ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ማኅበሩ በትምህርት ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች ከ5000 በላይ ፈሳሽ ሳሙናና የንፅህና መጠበቂያዎች ማሰራጨቱን የተናገሩት ዶ/ር መሸሻ፣ በቀጣይም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ የዝግጁነትና ምላሽ የድርጊት እቅድ አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከእህት ማኅበራት ጋር በመሆን 5000 የፊት ማስኮችን፣ 6000 ሰርጂካል ጓንቶችን፣ 1500 የህክምና ጫማዎችን፣ 1000 የፕላስቲክ የፊት መከላከያ እንዲሁም 5000 የመለያ ጋዋኖችን ለመግዛት በሂደት ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ከ500 በላይ የማኅበሩ አምቡላንሶችም ወገኖቻችንን ለማገልገል አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው እንዲጠባበቁ ተደርጓል ብለዋል፡፡