ማኅበሩ በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንና ደራሼ ልዩ ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አመራሮች በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንና ደራሼ ልዩ ወረዳ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ያሉበትን ሁኔታና ማኅበሩ በአካባቢው እያከናወነ ያለውን ሰብዓዊ ተግባራት አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አደረጉ፡፡
የማኅበሩ ብሔራዊ ቦርድ አባል ፕሮፌሰር አብርሃም ሃይለአምላክ በመስክ ጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ህብረተሰቡ ወደ ሰላማዊ ህይወቱ እንዲመለስ እየሰራ ነው፡፡ ማኅበሩ ሰብዓዊ ተግባራቱን ለአካባቢው ማኅበረሰብ በትኩረት መስራት እንዲያስችለው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ሌላኛው የቦርድ አባል አቶ ኢያሱ ኩምሳ በበኩላቸው በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የተከሰተው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ችግሩን ለመቅረፍ ለሶስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለማድረግና ለ16 ወራት የሚቆይ መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት ከአጋር እህት ማኅበራት ጋር ቀርፆ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የማኅበሩ አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አየለ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ በአካባቢው መፈናቀል ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ወደ 4,000 ለሚጠጉ አባዎራዎች ከዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
ማኅበሩ ከስዊስ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር 12,000 አባዎራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰባት ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ አስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ መፈራረሙን የተናገሩት አቶ ዳንኤል፣ በቀጣይም ከኔዘርላንድ ቀይ መስቀል ጋር በመሆን አደጋ የመቋቋም አቅማቸውን ለመገንባት ወደ 12 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ፕሮጀክት ፀድቆ ወደ ተግባር ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡