ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሜቴ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአምቡላንስ ድጋፍ አደረገ።


ድጋፉ በአገሪቱ የተለያየዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ አምቡላንሶችን ለመተካት ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።
ሐምሌ 03፣2017 አዲስ አበባ
የኢትዮጵየ ቀይ መስቀል ማኅበር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በድጋፍ የተበረከቱለትን 14 አምቡላነሶች ዛሬ ተረክቧል፡፡የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሓፊ አቶ አበራ ሉሌሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በኢትጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና በአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ መካከል ያለው አጋርነት አመታትን የተሻገረና በመጠንም በስፋትም እያደገ የመጣ መሆኑን አንስተዉ ኮሚቴው የማህበሩን የሎጀስቲክስ አቅም በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የኢትጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ንብረት የሆኑ አምቡላንሶች፤ቢሮዎች፤መገልገያ ቁሳቁሶችና ሌሎች ንብረቶች መውደማቸዉን ያስታወሱት አቶ አበራ በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ ግን ዳግም ወደ ስራ መግባት ተችሏል ብለዋል፡፡ለዚህም ለኮሚቴው ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተወካይ አቶ ዘውዱ አያሌው በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፡ ድጋፉ ማኅበሩ እየሠጠ ያለውን ህይወት የማዳን ተግባር በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ለመስጠት ያስችለዋል ያሉ ሲሆን ትብብሩ በአጋርነት መንፈስ ይቀጥላልም ብለዋል።አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ያላቸው ትብብር ብዙ መልክና ገፅታ ያለው ነው ያሉት ተወካዩ ፤ይህ የአምቡላስ ድጋፍም በሁለቱ ሰብዓዊ ተቋማት መካክል ለዘመናት የዘለቀው የትብብርና የአጋርነት መንፈስ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አዲስ አለም ሙላት በዚሁጊዜ ቦርዱን በመወከል ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላለፉት 90 ዓመታት በሰብዓዊ ተግባራት ላይ በመሰማራት ህብረተሰቡን ሲያገለግል መኖሩን አስታውሰው፤በድጋፍ የተገኙት አምቡላንሶች የማህበሩን ህይወት የማዳን ተልዕኮ በማገዝ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብልዋል፡፡

በኢትዮጵየ ቀይ መስቀል ማኅበር የአደጋ ስጋት ስር አመራር መምሪያ ተወካይ የሆኑትአቶ ጋሻው ዳኜ በርክክቡ ወቅት ባስተላፉት መልዕክት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ማህበሩን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ አስተዋፅዎ አድንቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከ7መቶ በላይ አምቡላንሶችን በመላው አገሪቱ በማሠማራት የህይወት አድን ተግባሩን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵየ ቀይ መስቀል ማህበር ፤ በድጋፍ ያገኛቸውን አምቡላንሶች በአማራ፤ኦሮሚያ፣ጋምቤላ፣ደቡብ ኢትዮጵያ፣ሀረሪና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለሚገኙ የማህበሩ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች አስተላልፏል።
ከቀናት በፊት 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በድምቀት ያከበረው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የአምቡላስ አገልግሎት የጀመረው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1944 ዓ.ም ነበር።ማህበሩ ላለፉት ዓመታት በሚሰጠው የ24 ሰዓት ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት ህይወት የመታደግ ተልዕኮውን በትጋት እየተወጣም ይገኛል፡፡
