ማኅበሩ ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸሙን መገምገም ጀመረ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ2017 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸሙን የብሔራዊ ማኅበሩና የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየገመገመ ነው፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፕሮጀክቶች አፈጻጸም በኩል ከዕቅድ በላይ ውጤት እንደተመዘገበ የተገለፀ ሲሆን አባላትን ከማበራከትና ገቢ ከማሰባሰብ አኳያ ውስንነቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ አበራ ሉሌሳ በማኅበሩ ብሄራዊና የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የዕቅድና የሪፖርት አሰራር ስርዓት መከበር እንዳለበት ያሳሰቡ ሲሆን ማኅበሩ ፖሊሲዎች፤ የአሰራር መመሪያዎችንና ማኑዋሎችን አዘጋጅቶ በስራ ላይ በማዋል ረገድ በርካታ አበረታች ስራዎች መስራቱን ገልጸው አሰራሮችን ዲጂታላዊ በማድረግ በኩል ግን ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋልዋል፡፡
በየጊዜው እየተከሰቱ ያሉት ሁኔታዎች በሰብዓዊ አገልግሎት ስራው ላይ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥሩ ሆነዋል ያሉት ዋና ጸሐፊው ከተለምዷዊው አሰራር በመውጣትና ተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን በማካሄድ የማኅበሩን ህልውና ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብላዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የዕቅድ አፈጻጸፈም ሪፖርቱ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም በሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በነገው ዕለትም በማኅበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ዙሪያ ማብራሪያና ውይይት እንደሚደረግም የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም የአቅም ግንባታ አውደ ጥናት እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው ፡፡