ማኅበሩ የዓለም የአእምሮ ጤና ቀንን አከበረ


የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በየዓመቱ በመላው ዓለም መስከረም 30 ቀን የሚከበረውን የዓለም የአእምሮ ጤናቀን የማኅበሩ አመራር አካላት፣ ሠራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የእህት ብሔራዊ ማኅበራት እንዲሁም የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና የአለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ፌዴሬሽን ተወካዮች በተገኙበት ‘‘የአገልግሎት ተደራሽነት ፡የአእምሮ ጤና በአደጋዎችና በድንገተኛ ሁኔታዎች’’ በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡ዕለቱ ማኅበሩ የአዕምሮ ጤናን የአደጋ ዝግጁነትና መልሶ ማቋቋም ተልዕኮዎቹ ዋና አካል አድርጎ እንዴት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው ለመወያየት ወሳኝ አጋጣሚ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የማኅበሩ የሰው ሃብት፣ ንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት መምሪያ ኅላፊ ተወካይ የሆኑት አቶ ሳሙኤል አበበ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፣ ማኅበሩ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተወሰኑ ክልሎች የአእምሮ ጤና ተግባራትን ሲያደርሰ መቆየቱን አስታውሰው፣ የእእምሮና የስነልቦና ጤና ድጋፉን ቀሰ በቀስ ስርዓታዊ በሆነ መንገድ ወደ ብሔራዊ መስሪያ ቤትና ወደ ከልል ቅርንጫፎቻችን በማዋሃድ ተደራሽነትን እያሰፋ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሳሙኤል አክለውም፣ ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በአደጋ ምላሽና ፍልሰት ፕሮግራሞቹ ውስጥ ማኅበረሰብ ተኮር የአእምሮ ጤናና ስነልቦናዊ ድጋፍ ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው መሪ ቃል የአዕምሮ ጤና ችግሮች በብዛት ሊከሰቱባቸው የሚችሉባቸውን አካባቢዎች ለማጉላት፤ ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል ብዙዎቹ ሙያዊ የአእምሮ ጤና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና አስፈላጊው ድጋፍ ወደ እነርሱ መድረስ እንዳለበት ለማሳየት ይረዳልም ብለዋል፡፡

የአእምሮ ጤና ድጋፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገንዘብ ድጋፍ ዕጥረት ቀውስ እንደገጠመው ያነሱት በማኅበሩ የአእምሮ ጤናና የስነ ልቦና ድጋፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አዲሱ አለባቸው፣ በዓለም ላይ ካለው አጠቃላይ የጤና በጀት ውስጥ 2 በመቶው ብቻ ለአእምሮ ጤና እንደሚመደብ አስታውሰው በዚህ ምክንያትም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሲያገኙ የነበረው አገልግሎት አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል፡፡

የአእምሮ ጤናና ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ድጋፍ (MHSSS)ምርጫ ሳይሆን ህይወት አድን ተግባር ነው ያሉት አቶ አዲሱ ትኩረታችን በማህበረሰብ ደረጃ ላይ የተመሰረተ የአእምሮ ጤናና ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ድጋፍ መስጠትና ይህ ወሳኝ ድጋፍ ለሁሉንም ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ብለዋል፡፡
ዕለቱ በተለያዩ ትምህርታዊና አዝናኝ መርሃ መርሃ ግብሮች ተከብሯል፡፡