ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዓመታዊ ግምገማውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ለሶስት ቀናት የቆየውን የ2017 በጀት ዓመት እንዲሁም የ2018 1ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ከጥቅምት 11-13 ቀን 2017 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል።

የቀድሞው የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የአሁኑ የብሔራዊ ማኅበሩ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ መሐመድ ጀማል አባቦራ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ያስመዘገባቸውን የጋራ ውጤቶች የገለጹ ሲሆን የሰብዓዊ አገልግሎት ልህቀትን ዕውን ለማድረግ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችን አበረታተዋል፡፡

የዞኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎችም አቶ መሐመድ በኃላፊነት በቆዩባቸው ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ለማኅበሩ ላሳዩት ቁርጠኛ አመራርና ለድርጅቱ ላበረከቱት አስተዋፅዖ እውቅና በመስጠት በክብር አሸኛኘት አድርገዋል።

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ከማል አብደላ ከአቶ መሀመድ ጀማል ጋር በመሆን በርካታ ጠቃሚ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን ፤ የክልልን ቅርንጫፍ ጽ/ ቤቱን የወደፊት አፈጻጸም ለማጠናከር መሻሻል ያለባቸውን ቁልፍ ጉዳዮችም በአጽንኦት አንስተዋል።
ከውይይቱ ጎን ለጎንም የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ቲም-ቸርተር ስምምነት ከዞን ጽ/ቤቶች ጋር ተፈርሟል።

በመጨረሻም በማኅበሩ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሁሉም ተሳታፊዎች፣ ሰራተኞችና አመራሮች ላበረከቱት ለሰብዓዊ አገልግሎት እና ለማኅበሩ ልህቀት ላሳዩት ቁርጠኝነት ልባዊ ምስጋና አቅርቧል።