ወጣቶች በግጭት ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡትን ድጋፍ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አስረከቡ
የቀድሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የኢትዮጵያ ወጣት ለሰላም ማህበር በትግራይ ክልል በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያሰባሰቡትን ድጋፍ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አስረክበዋል፡፡ የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም በማህበሩ በኩል ለተጎጂዎች በቀጥታ እንዲደረርስ የተሰጠው ድጋፍ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትና የምግብ፣ የአልባሳት፣ የህጻናት አልሚ ምግቦችና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የቀድሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት አቶ አቢዮት በላቸው ‹‹ይህንን ድጋፍ ያደረግነው ለትግራይ ህዝብ ያለንን ወገናዊነት ለመግለጽ ነው›› ብለዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን መሰል ድጋፍ ለማድረግ የተሳተፉትን ጓደኞቻቸውንና የኢትዮጵያ ወጣት ለሰላምና ለልማት ማህበር አባላትና በጎ ፈቃደኞችን አመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣት ለሰላምና ለልማት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቦና ደበላ በበኩላቸው ‹‹የቀድሞ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ጥሪ ተቀብለን አባላቶቻችንንና በጎ ፈቃደኞቻችንን በማስተባበር ይህንን ድጋፍ ማድረግ በመቻላችን ደስታ ተሰምቶኛል፡፡›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣይም በሁሉም የሃገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል ድጋፉን የተረከቡት የማኅበሩ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ እንግዳ ማንደፍሮ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በራስ ተነሳሽነት የሚደረጉ መሰል ድጋፎች አጋርነትን ከማሳየት ባለፈ እንደ ሃገር ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ አቶ እንግዳ አክለውም ሌሎች የማህበረሠቡ ክፍሎች በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመደገፍ እጆቻቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከለጋሾች የተበረከተው ድጋፍ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አማካኝነት ለሚመለከታቸው ተጎጂዎች በቀጥታ እንደሚደርስ ማኅበሩ ገልጿል፡፡
በቀጣይ መርዳት ለምትፈልጉ፡- በኢ.ቀ.መ.ማ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000327016559 (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) በኩል ማገዝ ይችላሉ፡፡