ማኅበሩ በ2012 በጀት ዓመት ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሰብዓዊ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በ2012 በጀት ዓመት ከ728 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ፣ በ537 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሰብዓዊ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ፡፡ የሰብዓዊ አገልግሎት ተግባራቶቹ በዋናነት በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) መከላከል፣ በአደጋ ምላሽ እና አደጋ መቋቋም ዙሪያ የተከናወኑ ናቸው፡፡
የማኅበሩን የ2012 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የማኅበሩ ተጠባባቂ ዋና ፀሀፊ አቶ አበራ ሉሌሳ እንዳሉት፣ ወደ 36 ሚሊዮን ለሚሆኑ ወገኖች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የእጅ ማፅጃ ቁሳቁሶች ስርጭት እና የሙቀት ልኬት ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በ5,701 ተቋማት የፀረ ተህዋሲ ርጭት ተከናውኗል፡፡
ማኅበሩ ከኮካ ኮላ ፋውንዴሽን በተገኘ 6.3 ሚሊዮን ብር፣ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት እና ከወጋገን ባንክ በዓይነትና በብር በተገኙ የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፎች በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ተፅዕኖ ላሳደረባቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 1,500 የጎዳና ተዳዳሪዎች ለ60 ቀናት የምገባ መርሀ ግብር ማከናወኑን እንዲሁም ከኔዘርላንድ ቀይ መስቀል ማኅበር በተገኘ 1.6 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለሌሎች 1,500 አባ/እማ ወራዎች የምግብና የዘይት እደላ ድጋፍ ማድረጉን ተ/ዋና ፀሀፊው ተናግረዋል፡፡ በለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 3,500 ወገኖችም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጋቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ በአደጋ ምላሽ ተግባራቱ ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የአምቡላንስና የመጀመሪያ ህክምና አገልግሎት፣ ለ3.5 ሚሊዮን ወጎኖች የመሰረታዊ መድኃኒት አቅርቦት፣ ለ1,552 ከሳውዲና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተመላሾች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ለሚገኙ 120 ተፈናቃይ ወገኖች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም በግጭት ምክንያት ለተጎዱ 210,179 ወገኖች የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አቶ አበራ ገልፀዋል፡፡ በአደጋ መቋቋም ተግባራቱም እንዲሁ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ወገኖችን በልዩ ልዩ የአደጋ መቋቋም ተግባራት ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ወደ አምስት ሚሊዮን ወገኖችን ደግሞ በማኅበረሰብ ንቅናቄና ወረርሺኝ መከላከል፣ በጤና፣ በውሃና ስነንፅህና ማስተዋወቅ ተግባራት ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በበጀት ዓመቱ የሰብዓዊ አገልግሎቱን የሚደግፉ አዳዲስ 1,256,405 አባላትን አፍርቷል፡፡ ማኅበሩ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን የሰብዓዊ አገልግሎት ተግባራት ያከናወነው 222,000 አዳዲስ በመለመላቸውና ነባር የቀይ መስቀል በጎፈቃደኞቹን በማሰማራት መሆኑን ተ/ዋና ጸኃፊ አቶ አበራ ሉሌሳ ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዋሽ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ 300 አባወራዎች ከፊንላንድ ቀይ መስቀል በተደረገ ድጋፍ 390 የስንዴ ዱቄት፤ ሩዝ፤ ሞኮሮኒና ፓስታ መታደሉን፤ አሁንም በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በአዋሽና አሚባራ አካባቢ እንዲሁ ከዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት (Global Alliance for the Rights of Ethiopians) በተገኘ አንድ ሚሊዮን ብር የተገዛ 353.5 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና 2,343 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ በመደረግ ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡም በደቡብ ክልል በተከሰተ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ 1,700 ወገኖች የሚውል 170 ኩንታል ሞኮሮኒና ፓስታ እንዲሁም 170 ሊትር የምግብ ዘይት ወደ አካባቢዎቹ መላኩን ተ/ዋና ፀኃፊው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሰብዓዊ ተግባራቶቹን የሚያከናውነው ከግል የፋይናንስና የቢዝነስ ድርጅቶችና ተቋማት፣ ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች፣ ከእህት ማኅበራት፣ ከአገር በቀል ሰብዓዊ ድርጅቶች፣ ከአባላትና በጎፈቃደኞች እንዲሁም ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡