ማህበሩ ከታወቂ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ህብረተሰባችን ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረበ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከታዋቂ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን #ኪነ-ጥበብ ለሰብዓዊነት; በሚል የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የአዲስ አበባን ህብረተሰብ የማንቃትና የማስተማር የንቅናቄ ዘመቻ አደረገ፡፡
በዚህ የህብረተሰብ ማንቃትና የማስተማር ንቅናቄ ላይ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉት የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ፣ የኢትዮ-ጃዝ ሙዚቃ ሳይንስ ፈጣሪ የሆኑት ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ፣ ታዋቂው የሥነ ጽሁም መምህርና ባለሙያ አቶ አያልነህ ሙላቱ፣ አንጋፋው ሙዚቀኛ አቶ አለማየሁ እሸቴ እንዲሁም ታዋቂው ተዋናይ እና የማኅበሩ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቦርድ አባል የሆነው አቶ ፋንቱ ማንዶዬ ናቸው፡፡
የህዝብ ንቅናቄው መርሃ ግብር ያተኮረው ከፍተኛ የህዝብ መጨናነቅና መተፋፈግ የሚስተዋልባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ክፍሎች ላይ ነው፡፡ ቦታዎቹም በዋነኝነት በመርካቶ፣ አውቶብስ ተራ፣ መሳለሚያ፣ ተክለሃይማኖት፣ አትክልት ተራ፣ ጊዮርጊስ፣ ሽሮ ሜዳ፣ አራት ኪሎና 6ኪሎ እንዲሁም በሠንጋተራና ለገሃር አካባቢ ነው፡፡ እነዚህ አንጋፋ የሥነ ጥበብ ሰዎች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአቀረበላቸውን ወቅታዊ ጥሪ እድሜያቸው ሳይገድባቸው ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ህብረተሰቡ የአካል ፈቀቅታውን በሁለት የአዋቂ እርምጃ በመገደብ፣ የአካል ንኪኪን በማስቀረት፣ ሠላምታ በእጅና በአካል በመነካካት መለዋወጡን በመተው በቀደመውና ባህላችን በሆነው ‘እጅ መንሳት’ እንዲለዋወጥ፣ እጅንም አዘውትሮ በሳሙና እንዲታጠብ ተማጽነዋል፡፡ የማስተማሪያና የማንቂያ ጽሁፎችን ለህዝቡ አድለዋል፡፡ የእጅ ማጽጃ አልኮል በመጠቀም የሚወዳቸውንና የሚያከብራቸውን፣ እነርሱም አጥብቀው የሚወዱትና የሚያከብሩት ህዝብ በዚህ አደገኛ የኮረና ቫይረስ ህይወቱ እንዳይቀጠፍ እጆቹን በአልኮል በማጽዳት ጭምር፣ ምክራቸውን፣ ምህላቸውንና አዛውንታዊ ተማጽኗቸውን ቀኑን በሙሉ ሳይታክቱ በማቅረብ የህዝብ ተቆርቋሪነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የኢትዮ-ጃዝ ሙዚቃ ሳይንስ ፈጣሪ የሆነው ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ በመልዕክቱ፣ #የፈጠራ ሥራዬን የሚያዳምጥልኝ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ህይወት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲጠበቅልኝ ስለምፈልግ እራሳችሁን፣ ቤተሰባችሁንና መላው ወገኖቻችሁን ከኮሮና ቫይረስ ጠብቁ; ብሏል፡፡ የሥነ ጽሁፍ ባለሙያው አያልነህ ሙላቱ በበኩሉ የምጽፈውን ሥነ ጽሁፍ የሚያነብልኝ፣ የምሰጠውንም ትምህርት የሚማርልኝ ወገኔ ጤንነቱ እንዲጠበቅ የራሱን፣ የቤተሰቡን እና የመላ ወገኑን ህይወት ከኮሮና ቫይረስ ይጠብቅ በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
አንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴና ታዋቂዉ ተዋናይ ፋንቱ ማንዶዬ ደግሞ እንዲሁ ህብረተሰቡ በሚጓዝበት፣ በሚገበያይበት እንዲሁም በእምነት ተቋማቶች ውስጥ ፀሎት በሚያደርግበት ወቅት ከንክኪ በፀዳ መንገድና ርቀቱን በሁለት የአዋቂ እርምጃ በማድረግ ራሱንና ወገኑን ከኮረና ቫይረስ ጥቃት እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የኮረና ቫይረስ ወረርሺኝ በሀገራችን መከሰቱ ከተሰማበት ዕለት አንስቶ ከብሄራዊ ጽ/ቤት እስከ ቀበሌ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መዋቅሩ የኮረና ቫይረስ ስርጭት መከላከል ግብረ ኃይል በማዋቀር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ህብረተሰቡ እጁን እንዲታጠብ የማድረግ እና ሰዎች በብዛት በሚሰባሰቡባቸው አካባቢዎች ርቀታቸውን በመጠበቅ ከንክኪ እንዲታቀቡ የማስገንዘብ ሥራዎችን በሁሉም ክልሎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ማህበሩ ለጤና ሚኒስቴር የተለያዩ የንጽህና መጠበቂ ቁሳቁሶችን ያበረከተ ሲሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ የዝግጁነትና ምላሽ የድርጊት እቅድ አዘጋጅቶ ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከእህት ማኅበራት ጋር በመሆን 5000 የፊት ማስኮችን፣ 6000 ሰርጂካል ጓንቶችን፣ 1500 የህክምና ጫማዎችን፣ 1000 የፕላስቲክ የፊት መከላከያ እንዲሁም 5000 የመለያ ጋዋኖችን ለመግዛት በሂደት ላይ እንደሚገኝና ከ500 በላይ አምቡላንሶቹም ለዚሁ አገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ቀደም ብሎ ያስታወቀ ሲሆን ለበሽታው ምላሽ የሚሆኑ በርካታ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ከአጋሮቹ ያሰባሰበ ሲሆን እነዚህን ቁሳቁሶች በቅርቡ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካል የሚለግስ መሆኑን የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ አስታውቀዋል፡፡