ኮካ ኮላ ኩባንያ ለማኀበሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
በሀገራችን ከፍተኛ አደጋ አየጋረጠ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አ.ማ /ኮካ ኮላ ኩባንያ/ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
መጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ድጋፉን አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የኮሮና ቫይረስ ዜናን በፈረንጆቹ ታህሳስ 2019 ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ቫይረሱ በህዝባችን ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ዝግጅት እያደረገ መቆየቱን የገለፁት የማኀበሩ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ፣ በተለይም ታዋቂ የሀገሪቷ አርቲስቶችን፣ የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ፈጣሪ ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ፣ ደራሲ አያልነህ ሙላቱ፣ አርቲሰት አለማየሁ እሸቴ፣ ፋንቱ ማንዶየ፣ ንዋይ ደበበንና አረጋኸኝ ወራሽን እንዲሁም በሲኒማ ኢንደስትሪው ታዋቂ የሆነውን አርቲስት መኮንን ለአከን በመያዝ በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የማኀበራዊ ንቅናቄ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ዋና ፀሐፊው ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ ማኀበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለማኀበሩ ይህንን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው ድጋፉን አስመልክተው በመላው የቀይ መስቀል አባላቶችና በጐ ፈቃደኞች ስም አመስግነዋል፡፡ ወደፊትም ኩባንያው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡
ማህበሩ የተገኘውን የገንዘብ እርዳታ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው በመዲናዋ ጐዳናዎች ላይ ወድቀው ለሚገኙ ወጣቶች፣ ሴቶችና አዛውንቶች የምግብ ድጋፍ እንደሚውልም ተመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የኮካ ኮላ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳረል ዊልሰን በበኩላቸው ኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ታሪክ ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን አመልክተው ኩባንያቸው ችግሩን ከግምት በመውሰድ ድጋፍ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን አቅም በፈቀደ ሁኔታ ከጎናቸው እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘው ኩባንያቸው የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮችንም ማምረትና ማከፍፈል እንደሚጀምር ገልፀው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቫይረሱን በትብብር ለመግታት እንዲቻል ሀኪሞች የሚሰጡትን መመሪያ መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ልክ እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ ወደፊትም ከኢትዮያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡