ማህበሩ ከታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረሰለሴ ጋር በመሆን ህብረተሰባችን ከኮሮና ቫይረስ ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላለፈ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የሁለት ኦሎምፒክ እና የአራት የአለም ሻምፒዮን ባለቤት ከሆነው ከታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር በመሆን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመዲናዋ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በመገናኛ፣ ተክለሃይማኖት፣ መርካቶና መሳለሚያ አካባቢዎች ላይ በመገኘት ህብረተሰባችንን የማንቃት ዘመቻ ሚያዚያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም አካሄደ፡፡
ማኀበሩ ከተለያዩ አንጋፋ የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ጥበብ፣ የሙዚቃ እና የፊልም ተዋናዮች ጋር በመሆን ‘ለወገን ደራሽ ወገን ነው’ በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት ወር ጀምሮ እያካሄደ ያለውን ህብረተሰባችንን የማንቃት የቫይረሱን ወረርሽኝ አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ ቁልፍ መልዕክቶችን ማለትም ዜጐች አስገዳጅ ሁኔታ ካላጋጠማቸው በስተቀር ቤታቸው እንዲቆዩ ትምህርት የመስጠት፣ የሁለት አዋቂ እርምጃ በማድረግ የአካል ንክኪን እንዲያስቀሩ የመምከርና እጅን በውሃና በሳሙና አዘውትረው እንዲታጠቡ፣ አልኮልና ሳኒታይዘርን መጠቀምን እንዲተገብሩ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ማኀበሩ ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበሩ ያቀረበለትን ወቅትዊ ጥሪ በመቀበል ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የመዲናዋ ነዋሪዎች በብዛት በሚገኙበት በመርካቶ፣ አብነት፣ መገናኛ አካባቢዎች ላይ በአካል በመገኘት ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ መሠረታዊ መልዕክቶች ለህብረተሰባችን እንዲደርስ አድርጓል፡፡
በዚህ ህብረተሰባችንን የማንቃት ሥራ ላይ ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በተለይም መርካቶ ላይ “የኮሮና ቫይረስ በአሜሪካ በቀን ከሁለት ሺህ ሰው በላይ በዓለማችን ደግሞ ከስድስት ሺህ የሚልቅ ህይወት እየቀጠፈ ነው፤ እባካችሁ መተዛዘላችሁን ትታችሁ ርቀታችሁን ጠብቁ ይህ ካልሆነ ግን ወደ ፊት የሚከሰተው አደጋ የከፋ ነው” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ዋና ፀሐፊ ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋም በበኩላቸው ማኀበሩ ‘ለወገን ደራሽ ወገን ነው’ በሚል መሪ ቃል ከታዋቂ አርቲስቶች ጋር በመሆን የተጀመረውን ቫይረሱን አስቀድሞ የመከላከል ዘመቻ በተለይም ከሀገራችን ባህል የተወራረሰና ልናስቀረው ያልቻልነውን የአካላዊ ርቀትን ዜጐች በመተግበር ወረርሽኙ ከሚያደርሰው ጉዳት እንዲታደጉ የማድረግ ጥሪን በመዲናዋ ጨምሮ ማኀበሩ ባለበት በ11ዱም የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዋና ፀሐፊው አክለውም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ህብረተሰባችን ስለቫይረሱ ያለውን ግንዛቤ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ሥራዎች ጐን ለጐን በመዲናዋ ላሉ የጐዳና ተዳዳሪ ወጣቶች፣ ሴቶችና አረጋዉያን የምግብ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ቫይረሱ በሃገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የመንግስትን ጥሪ በመቀበልና ከመንግስትም ጐን በመቆም እንደዚህ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን ወደፊትም ይህንን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡