ለእየሩሳሌም መታሠቢያ ድርጅት በግጭት ለተጎዱ ወገኖች የ500 ሺ ብር ድጋፍ አበረከተ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በትግራይና በመተከል በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ የሚሆን የ500 ሺ ብር ስጦታ ሐሙስ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ለኢትጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስረክበዋል፡፡
መታሰቢያ ድርጅቱን በመወከል ስጦታውን ያስረከቡት የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበር በኩረ ምዕመናን ጌታሁን በሻህ እንደተናገሩት ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የልማትና የሰብዓዊነት ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት በግጭት ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙ የትግራይና መተከል ወገኖቻችን ጉዳይ ስላሳሰበን ይህን ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታዓ በበኩላቸው ማኅበሩ በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ በሚያደርገው ጥረት የግብረሰናይ ማህበራት፣ ግለሰቦች ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በዛሬው ዕለትም በትግራይና በመተከል የሚገኙ ተጎጂ ወገኖቻችንን ለመደገፍ ማህበራችን ላደረገው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ይህንን ድጋፍ ያደረገውን ለኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት አመስግነዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አያይዘውም ይህንን አርአያ በመከተል በአገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የሰብዓዊነት ወዳጆች እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
እርዳታ ማድረግ ለምትፈልጉ ፡- • በኢ.ቀ.መ.ማ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000327016559 (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ወይም
• የሰብአዊነት ድጋፍ ፈንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 1 000 000 902 008 በኩል ማገዝ ይችላሉ፡፡