ማኅበሩ 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኮሮናን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶች ልገሳ አደረገ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ኢቀመማ) 25 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ለኢፌዲሪ ጤና እና ትምህርት ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በማኅበሩ ዋና ፅህፈት ቤት በተካሄደው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለፀው 6400 ጋውኖች፣ 700 ሠርጂካል ጋውኖች እና 265 ሺህ ጓንቶች ለኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ተበርክቷል፡፡ በተመሳሳይ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴርም 512 ሺህ የሚታጠብ የፊት መሸፈኛ ተረክቧል፤ይሄም በብር ሲተመን 10 ሚሊዮን 240 ሺህ ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የማኅበሩ ዋና ፀሀፊ አቶ ጌታቸው ታዓ እንደተናገሩተ ኢቀመማ ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የቫይረሱ ጉዳት የመቀነስ ሥራ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን፤ ማኅበሩ በአዲስ አበባ እና በክልሎች ባካሄደው ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ሥራ በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተደራሽ እንዳደረገ ገልፀዋል፡፡ 5700 የሚሆኑ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን ፀረ ተህዋስያን የመርጨት፣ 1500 የጎዳና እና ደጋፊ የሌላቸው ነዋሪዎችን መመገብ እና በማገገሚያ እና ለይቶ ማቆያ የሚገኙ 3500 ሰዎችን ለ60 ተከታታይ ቀናት መመገብ ማኅበሩ ኮሮናን ለመከላከል በ2012 ዓ.ም ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶች ስርጭት፣ ለፅኑ ህሙማን የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠት እና ስለቫይረሱ ያለው ግንዛቤን ማጠናከር በ2013 ቀዳሚውን ትኩረት ተሰጥቶዋቸው እየተከናወኑ የሚገኙ የማኅበሩ ሰብዓዊ ተግባራት እንደሆኑም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴርን የወከሉት በሚኒስቴሩ የትምህርት ቤቶች መሻሻል ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዩሐንስ ወጋሶ በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከዚህ በፊት ከምንሰማው የስርጭት አሀዝ በከፍተኛ ደረጃ ባሻቀበበት ጊዜ ድጋፉ በመደረጉ አመስግነው፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎቹ ወረርሽኙ ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ በፍጥነት እንደሚሰራጭ ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሠናይት በየነ ሚኒስቴሩን ወክለው ልገሳውን ሲረከቡ እንዳሳሰቡት በአገራችን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁን ያለበት የስርጭት ፍጥነት በጣም አስጊ ነው፡፡ ህፃን፣ ወጣት ወይንም ተጓዳኝ በሽታ የለብንም ብለን መዘናጋት ስህተት እንደሆነ እና ማስክ በአግባቡ መጠቀም፣ አካላዊ እርቀትን እና የግልን ፅህናን መጠበቅ ሁሉም ሰው በዋናነት ሊተገብረው የሚገባ የመከላከያ መንገዶች እንደሆኑ አማካሪዋ አስረድተዋል፡፡ በዛሬው እለት የተደረገላቸውን ድጋፍ ለህክምና ተቋማት እንደሚሰራጩ ዶክተር ሠናይት ገልፀዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ እና የሰውን ህይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡