“በአለም አቀፍ ደረጃ የርሃብ አደጋ በአስከፊ ሁኔታ ሊባባስ ይችላል” – የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ቀይ ጨረቃ ንቅናቄ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የርሃብ አደጋ በአስከፊ ሁኔታ ሊባባስ እንደሚችል የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ቀይ ጨረቃ ንቅናቄ አስጠንቀቀ፡፡
በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና አለመረጋጋት ምክንያት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ140 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት የተዳረጉ ሲሆን ይህም የርሃብ መጠን በሚቀጥሉት ወራት በእጅጉ ሊያድግ ይችላል፡፡
ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ድንገተኛ አደጋዎች፣ የትጥቅ ግጭት፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እና የፖለቲካ መሰናክሎች መበራከት በዓለምአቀፍ ደረጃ ርሃብ ከጫፍ ጫፍ እየጨመረ ይገኛል ብሏል፡፡
በመሆኑም አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ሰቆቃው እየሰፋ ለሚሊዮኖች ህልፈት ምክንያት መሆኑ አይቀሬ መሆኑን ተናግሯል።
በግጭትና በአየር ንብረት ቀውስ ለምግብ እጥረት የተጎዱትን አካባቢዎች የምግብ ምርት ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራሮች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባም አስረድቷል፡፡
ከነዚህ የቀውስ አዙሪት ለማምለጥ የሥርዓት ማሻሻያ መደረግ እንዳለበትም ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን (IFRC) እና የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ከመጪው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድመው ያሳስባሉ።
የብዙ ሰዎችን የርሃብ ሰቆቃ ለመግታት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ብቻውን መፍትሄ አይሆንም ያለው ንቅናቄው በአንጻሩ የተቀናጀ እርምጃ እና በረጅም ጊዜ ዕቅድ የቅርብ ትስስር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።
ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በመንግሥታት፣ በግሉ ሴክተር፣ እና በሰብአዊና በልማት ቡድኖች ተጨማሪ ጥረቶች መደረግ አለባቸው ብሏል።
የ IFRC ፕሬዝዳንት ፍራንሲስኮ ሮካ ሁለት ደርዘን የአፍሪካ ሀገራት ባለፉት አሥርት ዓመታት በከፋ የምግብ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደፕሮዝዳንቱ ገለጻ በአፍሪካ ቀንድ በግጭቶች፣ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎች እና በበርሃ አንበጣ ምክንያት 22 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለርሃብ ተጋላጭ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
ይህ ርሃብ እ.ኤ.አ. በ2023 እንደሚባባስ ጠቁመው በአሁኑ ወቅት አፋጣኝ እርምጃ ከተወሰደ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ማዳን እንደሚቻል ፕሬዝዳንት ፍራንሲስኮ አስታውቀዋል።
በመሆኑም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መታደግ የሚያስችል አስቸኳይ ድጋፍ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የ ICRC ፕሬዝዳንት ፒተር ሞሬ በበኩላቸው ግጭት አርሶ አደሩ እህል እንዳይዘራና እንዳይሰበስብ የሚከለክል በመሆኑ ለርሃብ መከሰት ዓይነተኛ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ፒተር አያይዘውም በሰብአዊ ምላሽ መዋቅር ውስጥ የመቋቋም አቅምን መገንባት ምኞታቸው መሆኑን ገልጸው በግጭትና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የዜጎች ህይወትን በሚያሰቃዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከአምስት አመት በታች ከሆኑ ህጻናት መካከል ከሦስቱ አንዱ ሥር በሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የቀነጨረ ሲሆን በአንጻሩ በወሊድ ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ከአምስቱ ሴቶች ሁለቱ በደካማ አመጋገብ ምክንያት የደም ማነስ ችግር አለባቸው።
በሶማሊያ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ህጻናት ቁጥር በአምስት እጥፍ ጨምሯል። ባለፈው ወር በባይዶዋ የሚገኘው የቤይ ክልል ሆስፒታል 466 ህጻናትን የተቀበለ ሲሆን ይህም በነሀሴ 2021 የነበረበት 82 ነበር።
በአፍጋኒስታን በሶስት አስርት አመታት በትጥቅ ግጭት እና ኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት ምግብ የመግዛት አቅም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ከአገሪቱ ከግማሽ በላይ ወይም 24 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡
በተመሳሳይ በፓኪስታን በቅርቡ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ አስከትሏል። ከዚህ የቅርብ ጊዜ ጥፋት በፊት በሀገሪቱ 43 በመቶው ህዝብ የምግብ ዋስትና እጦት ላይ ነበር። አሁን የተራቡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
እንዲሁም በሶሪያ ከ2019 ጀምሮ የምግብ ዋስትና እጦት መጠን ከ 50 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሶሪያ ህዝብ ሁለት ሦስተኛው ወይም ከ 18 ሚሊዮን ውስጥ 12.4 ሚሊዮን የሚሆነው የዕለት ተዕለት የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት አይችሉም፡፡
በዩክሬን ያለው ዓለም አቀፍ የትጥቅ ግጭት ዓለም አቀፋዊ የምግብ እና የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ እያሳደረ ባለው ተጽእኖ በብዙ ሀገሮች የወደፊት ምርትን በእጅጉ አስተጓጉሏል። ለአብነት ያህል በምስራቅ አፍሪካ ለርሃብ ተጋላጭ ለሆኑ ህዝቦች የእህል አቅርቦቱ በሚፈለገው ደረጃ እየደረሰ አይደለም፡፡
IFRC እና የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ቡድኖችን ያቀፈው ቡድን በሁሉም የአለም ማዕዘናት በተለይ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ ማህበረሰብ ውስጥ እርዳታ እያደረሱ ነው።
ICRC በዚህ አመት በደቡብ እና በማዕከላዊ ሶማሊያ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከ150 ሺህ ለሚበልጡ ቤተሰቦች ጥሬ ገንዘብ በማከፋፈል የአንድ ወር ምግብ እንዲገዙ ረድቷል። በናይጄሪያ ተመሳሳይ ፕሮግራም 675 ሺህ ሰዎችን የረዳ ሲሆን ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ የሰብል ምርትን ወደነበረበት ለመመለስ የአየር ንብረት ስማርት የግብርና ግብአቶችን አግኝተዋል።