የማኅበሩ ሠራተኞች በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከአዲሱ ዋና ፀሀፊ ጋር ተወያዩ
ጥር 17፣ 2013 ዓ.ም ዋና ፀኃፊ ሆነው በድጋሚ ወደ ማኅበሩን የተቀላቀሉት አቶ ጌታቸው ታዓ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የዋናው ፅህፈት ቤት ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በማኅበሩ ማሠልጠኛ ማዕከል ከዋና ፀኃፊ አቶ ጌታቸው ታዓ ጋር ባካሄዱት የትውውቅ እና የምክክር መድረክ ማኅበሩን በሚመለከት ትኩረት ይፈልጋሉ ያሉዋቸው ጉዳዮችን አንስተው በጋራ መክረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ትውውቅ ያደረጉት አቶ ጌታቸው ታዓ፤ ከ1993-1997 ማኅበሩን በኃላፊነት መምራታቸውን እና በቀጣይም በዓለም ዓቀፉ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ፈዴሬሽን ውስጥ በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ላይ የተለያዩ አገራት በመዘዋወር ሠብዓዊነትን ሲያገለግሉ እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡ በመጨረሻም በዘርፉ ያካበቱትን ጠቃሚ እውቀት እና ልምድ ይዘው ሠብዓዊነትን አንድ ብሎ ወዳስጀመራቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በመመለሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡ ዋና ፀኃፊው አክለውም ያላቸውን ሙሉ አቅም እና ግዜ ተጠቅመው የማኅበሩን አገልግሎት እና ተደራሽነት ለማሻሻል እንደሚተጉ አስረድተው፤ ለሚጠበቀው የጋራ ውጤት ሁሉም የማኅበሩ ባልደረቦች በኃላፊነት ስሜት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ከሠራተኞች እና ከሌሎች ሥራ ኃላፊዎች የማኅበሩን ሥራ እንቅስቃሴ የተመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ በጎ ፈቃደኞች እና አባላት ፣ የአምቡላንስ አገልግሎት እና የማኅበሩ ሀብት አሰባሰብ ትኩረት ካገኙ ሀሳቦች መካከል ናቸው፡፡ ማኅበሩ በበጎፈቃደኞች እና አባላት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ የምልመላ እና አስተዳደር ሥራው ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሰጠው በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ማኅበሩ ከሚያከናውናቸው ሠብዓዊ ተግባራት መካከል የአምቡላንስ አገልግሎት ዋነኛው ነው፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ የወደሙ እና የት እንዳሉ የማይታወቅ ጥቂት የማይባሉ አምቡላንሶች እንዳሉ፤ ሁኔታው ማኅበሩ የሚከተላቸውን መርሆዎች መሠረት አድርጎ የሚሠጠውን አገልግሎት እንዲስተጓጎል አድርጓል፡፡ ችግሩን በመሠረታዊነት ለመቅረፍ ትምህርተ ቀይ መስቀል ከታች ለሚገኘው የመንግስት መዋቅር እና ለሚመለከታቸው የህብረተሰቡ ክፍሎች አጠናክሮ መስጠት እንደሚገባ ዋና ፀሀፊው አመላክተዋል፡፡
በመጨረሻም ማኅበሩ የቆመለትን ዋና ዓላማ ‹ሰብዓዊነት› ማዕከል በማድረግ በተፈጥሮም ሆነ ሠው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች ያለምንም ልዩነት ህዝብን ለማገልገል ቃል በመግባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡